፲፬
 ፩ በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥  ፪ ለሎሌዎቹም። ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።  ፫ ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤  ፬ ዮሐንስ። እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና።  ፭ ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው።  ፮ ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤  ፯ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት።  ፰ እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው።  ፱ ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤  ፲ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው።  ፲፩ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው።  ፲፪ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት።  ፲፫ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት።  ፲፬ ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።  ፲፭ በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት።  ፲፮ ኢየሱስም። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው።  ፲፯ እነርሱም። ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት።  ፲፰ እርሱም። እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው።  ፲፱ ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ።  ፳ ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።  ፳፩ ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።  ፳፪ ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።  ፳፫ ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።  ፳፬ ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር።  ፳፭ ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።  ፳፮ ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ። ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ።  ፳፯ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።  ፳፰ ጴጥሮስም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው።  ፳፱ እርሱም። ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።  ፴ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ።  ፴፩ ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና። አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።  ፴፪ ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ።  ፴፫ በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት።  ፴፬ ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ።  ፴፭ የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤  ፴፮ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።