፪
 ፩ ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል።  ፪ በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?  ፫ ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥  ፬ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።  ፭ ስለ እርሱ የምንናገርበትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና።  ፮ ነገር ግን አንዱ በአንድ ስፍራ። ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ወይስ ትጎበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?  ፯ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው፤  ፰ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት ብሎ መሰከረ። ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አናይም፤  ፱ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን።  ፲ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና።  ፲፩-፲፫ ስለዚህም ምክንያት። ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም። እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም። እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም።  ፲፬-፲፮ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም።  ፲፯ ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።  ፲፰ እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።