፲፭
 ፩ በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና።  ፪ ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት።  ፫ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?  ፬ እግዚአብሔር። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤  ፭ እናንተ ግን። አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥  ፮ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።  ፯ እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ።  ፰ ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤  ፱ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።  ፲ ሕዝቡንም ጠርቶ። ስሙ አስተውሉም፤  ፲፩ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው።  ፲፪ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው። ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት።  ፲፫ እርሱ ግን መልሶ። የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።  ፲፬ ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ።  ፲፭ ጴጥሮስም መልሶ። ምሳሌውን ተርጕምልን አለው።  ፲፮ ኢየሱስም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን?  ፲፯ ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን?  ፲፰ ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው።  ፲፱ ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና።  ፳ ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።  ፳፩ ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ።  ፳፪ እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች።  ፳፫ እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት።  ፳፬ እርሱም መልሶ። ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ።  ፳፭ እርስዋ ግን መጥታ። ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት።  ፳፮ እርሱ ግን መልሶ። የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ።  ፳፯ እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች።  ፳፰ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ። አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች።  ፳፱ ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ።  ፴ ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤  ፴፩ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።  ፴፪ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው።  ፴፫ ደቀ መዛሙርቱም። ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት።  ፴፬ ኢየሱስም። ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም። ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት።  ፴፭ ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤  ፴፮ ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ።  ፴፯ ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።  ፴፰ የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።  ፴፱ ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ።