፲
 ፩ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።  ፪ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።  ፫ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል። ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።  ፬ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ። ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው። ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።  ፭ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ።  ፮ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።  ፯ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥  ፰ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው።  ፱ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ።  ፲ ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤  ፲፩ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤  ፲፪ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት።  ፲፫ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።  ፲፬ ጴጥሮስ ግን። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ።  ፲፭ ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።  ፲፮ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ።  ፲፯ ጴጥሮስም ስላየው ራእይ። ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤  ፲፰ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን? ብለው ይጠይቁ ነበር።  ፲፱ ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ። እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤  ፳ ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው።  ፳፩ ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው? አላቸው።  ፳፪ እነርሱም። ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት።  ፳፫ እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ።  ፳፬ በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር።  ፳፭ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት።  ፳፮ ጴጥሮስ ግን። ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው።  ፳፯ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ።  ፳፰ አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤  ፳፱ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ አላቸው።  ፴ ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው። በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና።  ፴፩ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ።  ፴፪ እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል አለኝ።  ፴፫ ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።  ፴፬-፴፮ የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ።  ፴፯ ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ።  ፴፰ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤  ፴፱ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።  ፵ እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤  ፵፩ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።  ፵፪ ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን።  ፵፫ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።  ፵፬ ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።  ፵፭ ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤  ፵፮ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።  ፵፯ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ።  ፵፰ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።