፲፯
 ፩ በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ።  ፪ ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤  ፫ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ። ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ይል ነበር።  ፬ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ።  ፭ አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤  ፮ ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው። ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤  ፯ እነዚህም ሁሉ። ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ ብለው ጮኹ።  ፰ ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፥  ፱ ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው።  ፲ ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤  ፲፩ እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።  ፲፪ ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ።  ፲፫ በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ።  ፲፬ በዚያን ጊዜም ወንድሞቹ ወዲያው ጳውሎስን እስከ ባሕር ድረስ ይሄድ ዘንድ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስም በዚያው ቀሩ።  ፲፭ ጳውሎስን የሸኙት ግን እስከ አቴና አደረሱት፥ እንደሚቻላቸውም በፍጥነት ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ትእዛዝ ተቀብለው ሄዱ።  ፲፮ ጳውሎስም በአቴና ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት።  ፲፯ ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር።  ፲፰ ከኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢኮችም ከተባሉት ፈላስፎች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር ተገናኙ። አንዳንዶቹም። ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል? አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው። አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል አሉ።  ፲፱-፳፩ የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና።  ፳፪ ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ። የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ።  ፳፫ የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።  ፳፬ ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤  ፳፭ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።  ፳፮-፳፰ ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።  ፳፱ እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።  ፴ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤  ፴፩ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።  ፴፪ የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን። ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።  ፴፫ እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።  ፴፬ አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።