፬
 ፩ እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤  ፪ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤  ፫ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።  ፬ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤  ፭ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤  ፮ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።  ፯ ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።  ፰ ስለዚህ። ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።  ፱ ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው?  ፲ ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።  ፲፩ እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤  ፲፪-፲፬ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥  ፲፭ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤  ፲፮ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።  ፲፯ እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።  ፲፰ እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤  ፲፱ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።  ፳ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤  ፳፩ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤  ፳፪ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥  ፳፫ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥  ፳፬ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።  ፳፭ ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።  ፳፮ ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤  ፳፯ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።  ፳፰ የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም።  ፳፱ ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።  ፴ ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ።  ፴፩ መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።  ፴፪ እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።