፫
 ፩ ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ፥  ፪ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።  ፫-፯ ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?  ፰ እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና።  ፱ አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።  ፲ ሕዝቡም። እንግዲህ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር።  ፲፩ መልሶም። ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ ይል ነበር።  ፲፪ ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው። መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት።  ፲፫ ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው።  ፲፬ ጭፍሮችም ደግሞ። እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም። በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው።  ፲፭ ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ። ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር፥  ፲፮ ዮሐንስ መልሶ። እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤  ፲፯ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል አላቸው።  ፲፰ ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤  ፲፱ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥  ፳ ይህን ደግሞ ከሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አገባው።  ፳፩ ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥  ፳፪ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።  ፳፫ ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥  ፳፬ የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥  ፳፭ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊም ልጅ  ፳፮ የናጌ ልጅ፥ የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥  ፳፯ የዮዳ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥  ፳፰ የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ የዮሳስ ልጅ፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥  ፳፱ የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥  ፴ የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥  ፴፩ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ  ፴፪ የዳዊት ልጅ፥ የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥  ፴፫ የነአሶን ልጅ፥ የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥  ፴፬ የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥  ፴፭ የናኮር ልጅ፥ የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥  ፴፮ የቃይንም ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥  ፴፯ የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥  ፴፰ የመላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ።