፭
 ፩ ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፥ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤  ፪ በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር።  ፫ ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር።  ፬ ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን። ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው።  ፭ ስምዖንም መልሶ። አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው።  ፮ ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ።  ፯ በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው።  ፰ ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ። ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው።  ፱ ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥  ፲ እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን። አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው።  ፲፩ ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት።  ፲፪ ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የሞላበት ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም አይቶ በፊቱ ወደቀና። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ፥ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው።  ፲፫ እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው።  ፲፬ እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን። ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው።  ፲፭ ወሬው ግን አብዝቶ ወጣ፥ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር፤  ፲፮ ነገር ግን እርሱ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር።  ፲፯ አንድ ቀንም ያስተምር ነበር፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችም ሁሉ ከኢየሩሳሌምም መጥተው የነበሩ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይቀመጡ ነበር፤ እርሱም እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት።  ፲፰ እነሆም፥ አንድ ሽባ በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ አግብተውም በፊቱ ሊያኖሩት ይሹ ነበር።  ፲፱ ስለ ሕዝቡም ብዛት እንዴት አድርገው እንዲያገቡት ሲያቅታቸው፥ ወደ ሰገነቱ ወጡ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከል በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት።  ፳ እምነታቸውንም አይቶ። አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።  ፳፩ ጻፎችና ፈሪሳውያንም። ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው ያስቡ ጀመር።  ፳፪ ኢየሱስም አሳባቸውን እያወቀ መልሶ። በልባችሁ ምን ታስባላችሁ?  ፳፫ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?  ፳፬ ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ብሎ፥ ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ነተሣ፥ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ አለው።  ፳፭ በዚያን ጊዜም በፊታቸው ተነሣ፥ ተኝቶበትም የነበረውን ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ።  ፳፮ ሁሉንም መገረም ያዛቸው፥ እግዚአብሔርንም አመስግነው። ዛሬስ ድንቅ ነገር አየን እያሉ ፍርሃት ሞላባቸው።  ፳፯ ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ ተመለከተና። ተከተለኝ አለው።  ፳፰ ሁሉንም ተወ፤ ተነሥቶም ተከተለው።  ፳፱ ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩ ከቀራጮችና ከሌሎች ሰዎች ብዙ ሕዝብ ነበሩ።  ፴ ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ። ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ።  ፴፩ ኢየሱስም መልሶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤  ፴፪ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።  ፴፫ እነርሱም። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ ምን ብዙ ይጦማሉ ጸሎትስ ስለ ምን ያደርጋሉ፥ ደግሞም የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ምን እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም? አሉት።  ፴፬ ኢየሱስም። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎችን ልታስጦሙ ትችላላችሁን?  ፴፭ ነገር ግን ወራት ይመጣል፥ ሙሽራውም ከእነርሱ ሲወሰድ ያንጊዜ፥ በዚያ ወራት ይጦማሉ አላቸው።  ፴፮ ደግሞም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው። የአዲስ ልብስ እራፊ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል ደግሞም አዲስ እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም።  ፴፯ ባረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳል፥ እርሱም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል።  ፴፰ አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።  ፴፱ አሮጌ የወይን ጠጅ ሲጠጣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ አሮጌው ይጣፍጣል ይላልና።