፲፱
 ፩ ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ።  ፪ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው።  ፫ ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት።  ፬ እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥  ፭ አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?  ፮ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።  ፯ እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት።  ፰ እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም።  ፱ እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው።  ፲ ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት።  ፲፩ እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤  ፲፪ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው።  ፲፫ በዚያን ጊዜ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው።  ፲፬ ነገር ግን ኢየሱስ። ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤  ፲፭ እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ።  ፲፮ እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው።  ፲፯ እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው።  ፲፰ እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥  ፲፱ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።  ፳ ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው።  ፳፩ ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው።  ፳፪ ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ።  ፳፫ ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው።  ፳፬ ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ።  ፳፭ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ።  ፳፮ ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።  ፳፯ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።  ፳፰ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።  ፳፱ ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።  ፴ ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።